አፄ ዮሐንስ አራተኛ/Emperor Yohannes IV ልጅ ካሳ መርጫ

Описание к видео አፄ ዮሐንስ አራተኛ/Emperor Yohannes IV ልጅ ካሳ መርጫ

Tekle Giyorgis:    • አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዳግማዊ/Emperor Tekle Giyor...  

አፄ ዮሐንስ አራተኛ
አፄ ዮሐንስ ንጉሰ ነገስት ከመሆናቸው በፊት ስማቸው ካሳ መርጫ ይባል ነበር። ካሳ የተወለደው ሀምሌ 4፣ 1829 በተምቤን ክፍለ ሀገር በማይ በሃ ሲሆን አባቱም የተምቤን ሹም መርጫ እና እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ወለተ ሥላሴ(ሲላስ) ነበሩ። ካሳም ዘሩን ከዘመነ መሳፍንት ታላቅ ጌቶች አገናኘ፤ እነዚህም፦ ራስ ሚካኤል ስሁል፣ ራስ ወልደ ሥላሴ፣ እና ደጃች ሳባጋዲስ ወልዱ ነበሩ። እናቱ ወይዘሮ ሲላስም የእንደርታ ደጃች እና የአጋሜዋ ወይዘሮ ታቦቱ ልጅ ነበሩ።
ካሳ ጉግሳ የተባለ ታላቅ ወንድምና ድንቅነሽ የተባለች ታላቅ እኅት ነበረችው፤ እርሷም ኋላ ላይ ከላስታው ዋግሹም ጎበዜ ገብረ መድኅን (አፄ ተክለ ጊዮርጊስ) ጋር ተጋብታለች።
ካሳ መርጫ በተወለደ ጊዜ ካሳ ኃይሉ(አፄ ቴዎድሮስ) የ14 ዓመት ልጅ ነበረ። አፄ ቴዎድሮስም ሥልጣን ይዘው በተጠናከሩ ጊዜ ካሳ መርጫ ለንጉሱ ተገዝቶ ነበር። ያገኘውም ማዕረግ ከኢትዮጵያ ባላባቶች ማዕረግ ሁሉ ትንሽ የሆነውን ባላምባራስ የሚለውን ማዕረግ ነበር። ካሳም ይህ ማዕረግ ምንም ያህል አላረካውም ነበር፤ በተለይም ደግሞ የ11 ዓመት ታናሹ የሆነው ሳህለ ማርያም (ዳግማዊ ምኒልክ) ንጉስ ከሚለው ማዕረግ በሁለት ደረጃ የሚያንሰውን ደጃዝማች የሚለው ማዕረግ በማግኘቱ ይህ ነገር የባሰ ሆነበት።
በዚህም ካሳ በ27 ዓመቱ በቴዎድሮስ ላይ አመፀ፤ ነገር ግን ቴዎድሮስ ከፍተኛ ሥልጣን ስለነበራቸው ካሳ ከተምቤን እና እንደርታ ወደ አጋሜ ክፍለ ሀገር አፋር ሸሸ። በዛም በቆየበት ወቅት ነበር አንዲት የአፋር ሴት አግብቶ ስሟን ወደ ክርስትያን ስም ቀይራ ጥበበ ሥላሴ የተባለችው፤ ከሷም ልጅ አርዓያ ተወለደለት። በ5 ዓመት ውስጥም በእድሜው 32 ዓመት የሞላው ካሳ በትግራይ ከፍተኛ ኃይል ያለው ሆነ፤ በሙሉ ልብም በአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ላይ የንጉሰ ነገስት ሥልጣን ይዞ ተነሳበት። በእውነታው ካሳ ከ1860-1861 በነበረው ጊዜ ውስጥ ካሳ በደንብ መሳርያ የታጠቁና በደንብ የሰለጠኑ ሰልፈኞች ነበሩት፤ እርሱም ደጃዝማች ሆነ እናም የተክለ ጊዮርጊስን ሠራዊት ለመጋጠም ዝግጁ ሆነ። በ1862 ተክለ ጊዮርጊስ ሠራዊታቸውን አንቀሳቀሱ፤ ወደ ትግራይም ለመዝመት አቀዱ፤ ነገር ግን ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት ሚስታቸው ድንቅነሽ ይህንን የትግርኛ ግጥም ብለው አስጠነቀቋቸው፦
ኣንቱም ሰባት ናብ ዓድዋ ኣይትኺዱ
ብእሳተ ጎመራ ከይትነዱ
ኣባ በዝብዝ ካሳ ቆራጽ እያ ኸብዱ
ተክለ ጊዮርጊስ ግን ሚስታቸውን አልሰሙም፤ ወደ አድዋም ዘመቱ፤ የካሳንም ጦር ገጠሙ፤ በተቀናቃኛቸውም እጅ ሽንፈት ተቀበሉ፤ በጊዜው ሻለቃ በነበሩት በራስ አሉላ እጅም እንደተማረኩ ይታመናል። ከተሸነፉና ከተማረኩም በኋላ ድንቅነሽ ዳግም በአማርኛ እንዲህ ብለው የሀዘን እንጉርጉሮ አንጎራጉረዋል፦
ተናግሬ ነበር እኔስ ኣስቀድሜ
ኣሁን ምን ልናገር ከሃዘን ላይ ቆሜ
የተሻረው ባሌ፡ ተሿሚው ወንድሜ
ከእንግዴህስ ወዲህ ኣልመኝም እድሜ
ከተክለ ጊዮርጊስ ሽንፈት በኋላ ካሳ ለንግሱ በዓል የሚሆነውን አስፈላጊውን ዝግጅት አደረገ። ንጉሰ ነገስት ከመባላቸውም በፊት ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሀገራት ዘንድ እውቅና እና ድጋፍ እንዲያገኙ ወደ አውሮፓ ሀገራት ደብዳቤዎች ልከው ነበር።
በደብዳቤውም ካሳ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን ነገስታት ጠቅሰዋል። በደብዳቤው ሚካኤል ብለው የጠቀሱት ሚካኤል ስሁልን ነው። ወልደ ሥላሴን በደብዳቤው የጠቀሱት ከፈረንሳዮች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስለነበረው ነው። ለንግስት ቪክቶርያም በላኩላት ደብዳቤ ላይ ከእንግሊዞች ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበረውን ሳባ ጋዲስን ጠቅሰዋል።
ካሳ ራሳቸውም የእንግሊዞች ጥሩ ወዳጅ ነበሩ፤ ቴዎድሮስ ከወደቁ በኋላም ጄነራል ናፒየር ለካሳ 12 ሞርታር ጠመንጃ፣ 900 ሽጉጦች እና ቁጥር አልባ ጥይቶች ነበር ሰጥቷቸው የሄደው። ናፒየርን ከሸኙ ከዓመት በኋላ እና ተክለ ጊዮርጊስን ከማሸነፉ ረጅም ጊዜ በፊት በቴዎድሮስ ጊዜ አስተርጓሚ የነበረውን ሳሙኤል ጊዮርጊስን እና ወርቄ መርጫን ወኪሎቹ ይሆኑ ዘንድ ወደ ለንደን ልኳቸው ነበር። ተክለ ጊዮርጊስንም ካሸነፈ በኋላ ወደ ንግስት ቪክቶርያ ደብዳቤ ላከ።
አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ከተሸነፉ በኋላ ለሙሉ ስድስት ወር የካሳ መርጫ የንግስና በዓል በዝግጅት ላይ ነበር። በጥር 18፤ 1864 ልክ እንደቀደመው የኢትዮጵያ ባህል ካሳ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለው በአክሱም በሚገኝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በአቡነ አትናቴዎስ ተቀቡ። Muse G. Douin እንዳለው ከሆነ ከንግስናው በዓል በኋላ ድግሱ ለሦስት ቀን ቀጠለ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ዜና መዋዕል ፀሐፊ የነበሩት አለቃ ዘዮሐንስ እንዳሉት ከሆነ ድግሱ ለሠላሳ ቀን የቆየ ነበር። ለታላላቅ ሰዎችና ለህዝቡ የቀረበው ምግብና መጠጥ ስንመለከት ግን የአለቃ ዘዮሐንስ ዘገባ ትክክል ሳይሆን አይቀርም። Dioun ራሱ እንደዘገበው 4000 በሬ ታርዶ ነበር፤ በ50 ትላልቅ ጋኖችም ማር መጥቶ በ150000 ብርሌዎች ጠጅ ተቀድቷል።
የንግስናው ድግስ በደንብ ተከናወነ፤ ነገር ግን ለአፄ ዮሐንስ አንድ ትልቅ ፈተና ነበረባቸው፤ ይህም በቴዎድሮስ ጊዜ የተጀመረውን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሂደት ማስቀጠል ፊታቸው ላይ ነበረባቸው። ዮሐንስ ከሀማሲን እስከ ሸዋ እንዲሁም እስከ ደቡቧ ጅማ ድረስ ለእርሳቸው እምቢተኛ የነበሩትን የአካባቢ ኃይሎች ለማስገዛት ወስነው ነበር።
እምቢተኛ ከነበሩት ተቀናቃኞች መካከል አንዱ የነበሩት የተክለ ጊዮርጊስ(ዋግሹም ጎበዜን) እኅት ወይዘሮ ላቀችን ያገቡት የጎጃሙ ራስ አዳል ነበሩ፤ ነገር ግን ዮሐንስ ያላቸውን ኃይል ለማሳየት በጎጃም ላይ ሲዘምቱ ራስ አዳል ያላቸውን የወታደራዊ ኃይል ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ሲያነፃጽሩ ከዮሐንስ እጅግ ያነሰ እንደሆነ ተገነዘቡ፤ በዚህም ምክንያት መልሰው ወደ ጫካው ሸሹ። ከዚህም በኋላ ዮሐንስ የቀደመውን የጎጃም ገዥ ደጃች ደስታን ራስ የሚለውን ማዕረግ ጨምረውለት ሾመውት ወደ መቀሌ ተመለሱ። ነገር ግን ራስ አዳል ከራስ ደስታ ጋር ተዋግተው በጦርነት ገደሉት። ለዮሐንስም ከእንግዲህ ወዲህ እንደሚገዙ እና ግብር እንደሚከፍሉ የሚናገር ደብዳቤ ላኩ፤ ንጉሰ ነገስቱም ተቀበሏቸው። መጀመርያ ላይ ዮሐንስ የአዳልን ጥያቄ አልተቀበሉም ነበር፤ ነገር ግን ግብፆች ኢትዮጵያን ለማጥቃት ዝግጅት ላይ እንደሆኑ ሲያውቁ አማካሪዎቻቸውን አማከሩና ጎጃምን ለራስ አዳል ሰጡ።
አፄ ዮሐንስ ለሦስት ዓመት ከነገሱ በኋላ አንድ የማድረጉ ሂደት የኢትዮጵያን መሬት በግብፅ ቃዲፍ ኢስማኤል ፓሻ ተስተጓጎለ። በ1867ም የኢትዮጵያና የግብፅ ሠራዊት ቦታቸውን በጉንደት ያዙ። የኢትዮጵያም ሠራዊት በሻለቃ አሉላ ትዕዛዝ ስር ሆነው በግራ መስመር የግብፅ ሠራዊትን ከበቡ፤ የአፄ ዮሐንስ ሠራዊትም በቀኝ በኩል ነበሩ፤ በመሃልና በኋለኛው ክፍል ደግሞ ብዙ ራሶች ነበሩ፤ ከእነርሱም መካከል የሀዜጋው/የሀማሲኑ ራስ ወልደ ሚካኤል ሰሎሞን አንዱ ነበሩ።
በጉንደት ጦርነት የተጠቀሙት የጦር ስልት የበሬ ቀንድ የጦር ሥልት ይባላል። በዚህም ሥልት ጠላት ይከበባል፤ ያመልጥ ዘንድም ጥቂት ክፍተት ይሰጠዋል። በዚህም የደጀን ጦር የተበተነውን ሠራዊት ይማርካል። የጉንደት ጦርነት የተጀመረው ከጠዋቱ 3 ሰዓት ነበር፤ የተጠናቀቀውም ከረፋዱ 9 ሰዓት ነበር። ሁለቱም ቡድን የተዋጉት በጀግንነት ነበር፤ እየመሩ የነበሩት ግን ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የዚህም ምክንያቱ የሜዳ ቦታ አያያዛቸው፣ የመሬት አጠቃቀም እውቀታቸው፣ የተጠቀሙት የጦርነት ሥልታቸው እና ደግሞ በታወቀ ሁኔታ የህዝብ ድጋፍ ስለነበራቸው ነበር።
የግብፅ ሠራዊትንም ደህና አድርገው ደመሰሱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩትንም ማረኩ፣ ሌሎች ደግሞ ሊያመልጡ ቻሉ፤ ነገር ግን ግብፆች በዚህ አላቆሙም በድጋሚም ሠራዊታቸውን አዋቀሩ፤ ከጉንደት ቅዥታቸውም አገገሙ፤ በ1869ም ሌላ የኢትዮጵያና የግብፅ ግጥምያ በጉራ ተካሄደ። በዚህ ጊዜም የግብፅን ሠራዊት እየመራ የመጣው የቃዲቭ ኢስማኤል ልጅ ሀሰን ፓሻ ነበር። በዚህም ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት 60000 ነበር፤ በዋናነት የተዋቀሩትም ከትግራይ፣ ከመረብ ምላሽ፣ ከጎንደር፣ ከጎጃምና ከሸዋ ነበር።

ማጣቀሻ(Reference)
1. https://www.africanidea.org/atse_yoha...
2. https://en.wikipedia.org/wiki/Yohanne...
3. https://en.wikipedia.org/wiki/Mikael_...
4. https://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8B%...

Комментарии

Информация по комментариям в разработке