እራስን ይቅር ማለት!

Описание к видео እራስን ይቅር ማለት!

እራስን ይቅር ማለት

ሣሙኤል ተክለየሱስ
==================================
ይቅርታ ብዙውን ጊዜ እንደበደለን በምናምነው ሰው ላይ የቁጣ ስሜትን ፣ ቂምን እና የበቀል ስሜትን ለመተው ሆን ተብሎ የሚወሰን ውሳኔ ነው። ይሄውም ሌሎችን ይቅር ለማለት በጣም ለጋስ የመሆን ችሎታን ይፈለጋል። ለራስ የሚደረግ ይቅርታ ግን እጅግ በጣም ከዚህ የተለየ ነው። ሁሉም ሰው ይሳሳታል፣ ነገር ግን ከእነዚህ ስህተቶች መማር ፣ ትላንትን መተው፣ ወደፊት መቀጠል እና እራስን ይቅር ማለት ለአእምሮ ጤና እና ደህንነት አስፈላጊ ነው።

እራስን እንዴት ይቅር ማለት ይቻላል?

ራስን ይቅር ማለት እራስን ማዋረድ ወይም የድክመት ምልክት አይደለም። ይቅር ባይ መሆን ወይም የበደለን ሰው ይቅር ማለት ምንጊዜም ቢሆን በህይወታችን አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን እኛ የጠፋውን እንደትክክል እንደሆነ እንቀበለዋለን፣ የሆነው ሁሉ ልክ ነው ፣ ወይም ልንለወጥ አንችልም ማለት አይደለም። ነገር ግን ባለፉ ክስተቶች ላይ ከመቆዘም ይልቅ ያለፈውን በይቅርታ በማለፍ የነገን ህይወት በተሻለ ተነሳሽነት ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው።

ራስን ይቅር ለማለት አራት ቁልፍ እርምጃዎችን መጠቀም እንችላለን። እነዚህም ራስን ይቅር የማለት መርሆዎች ብለን ልንጠራቸው እንችላለን፤ እነዚህም ፦

1- ኃላፊነት
2- ግምገማ
3- ተሃድሶ
4- ለውጥ

ኃላፊነትን መቀበል

እራስን ይቅር ማለት ያለፈውን ወደ ኋላ ከመተው እና ወደፊት ከመቀጠል የበለጠ ነገር ነው። የተከሰተውን መቀበል እና ለራስ ርህራሄ ማሳየት ማለት ነው። ያደረጉትን ወይም የተከሰተውን መጋፈጥ ራስን ይቅርታ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ከባዱ እርምጃም ይሄው ነው። ድርጊቶቻችን ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሰበብ እየፈጠሩ ፣ ምክንያታዊ ለመሆን በመጣር የውሸት ፅድቅን ከመሻት ይልቅ፣ ያደረግነውን፣ የተፈጠረውን ፊት ለፊት ለመቀበል ጊዜው አሁን መሆኑን መረዳት ነው።

ኃላፊነትን በመውሰድ እና የተፈጠሩትን ድርጊቶች በመቀበል ከልክ ያለፈ ጸፀትን እና የጥፋተኝነት ስሜት ባጠቃላይ አሉታዊ ስሜቶችን ማስወገድ ይቻላል።

ግምገማ

ኃላፊነት በመውሰዳችን ምክንያት የጥፋተኝነት እና የኃፍረት ስሜትን ጨምሮ የተለያዩ አሉታዊ ስሜቶች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። አንድ የተሳሳተ ነገር ስናደርግ፣ ስለእሱ የጥፋተኝነት ስሜት መስማት ሙሉ በሙሉ የተለመደ እና ጤናማ ነው። እነዚህ የጥፋተኝነት እና የፀፀት ስሜቶች ለአዎንታዊ የባህሪ ለውጥ እንደ መነሻ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማን መጥፎ ነገር የሠራን ጥሩ ሰው መሆናችንን ስለአመንን ነው። ኃፍረት ራስን እንደ መጥፎ ሰው እንድንመለከት ያደርገናል። ይህ በይቅርታ ካልተፈታ ወደ ድብርት እና እራስን ወደ መጉዳት ሊያመራ ይችላል።
የጥፋተኝነት ስሜት ሲሰማን ስህተቶች መጥፎ ሰው ሊያደርጉን ወይም ውስጣዊ እሴታችንን ሊያዳክሙ እንደማይችሉ ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል።

ጉዳቱን ማስተካከል እና አመኔታን ለመመለስ
የተፈጠረውን ስህት ማረም የይቅርታ አንዱ እና አስፈላጊው አካል ነው። በሆነ መንገድ እስክንገናኝ ድረስ ለሌላ ሰው ይቅር እንደማንል ሁሉ ፣ እራስን ይቅር ማለት እራስን እንዳገኘን ሲሰማን ሲሆን የመለወጥ ዕድላችን እጅግ ከፍተኛ ነው። ግለ ግምገማ ማድረግ ደግሞ ይሄንኑ እንድናሳካ ያግዘናል።

ተሀድሶ

ጥፋተኝነትን ለማለፍ አንዱ መንገድ ስህተቶችን ለማረም እርምጃ መውሰድ ነው። ይህ ሂደት እራስን በአዲሱ መንገድ እና በእድሳት ላይ ማተኮር ማለት ነው። ሁሉም ሰው ይሳሳታል በዚህም ምክንያት የምንቆጭበት ወይም የምንጸጸትበት ነገሮች ይኖራሉ ። በእብደት ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ፣ ራስን መጥላት ፣ አልፎ ተርፎም ለራስ ርህራሄ ማጣት ሊጎዳን እና ለራስ ያለንን አመለካከት እና ለመለወጥ ያለንን ተነሳሽነት እንድንጠራጠር እና ህይወታችንን አስቸጋሪ እንዳያደርግብን መጠንቀቅ ተገቢ ነው።

እራስን ይቅር ማለት ብዙውን ጊዜ ከልምዱ ለመማር እና እንደ ሰው ለማደግ መንገድ መፈለግን ይጠይቃል። ይህንን ለማድረግ እርስን ቆም ብሎ መጠየቅ እና ለምን የጥፋተኝነት ስሜት እንደተሰማን መረዳት የግድ ነው።

ለውጥ

ለወደፊቱ ተመሳሳይ ባህሪዎችን እንደገና ለመከላከል ምን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?

አዎ ! ዛሬ ምስቅልቅል ውስጥ ልንሆን እንችላለን፣ ነገር ግን ለወደፊቱ የተሻሉ ምርጫዎችን ለማድረግ የሚረዳ የመማሪያ ተሞክሮ ነበር ብሎ መቀበል ለራስ ይቅር ማለት ነው።

የስሜት ቀውስ ወይም ኪሳራ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምንም እንኳን በተፈጠሩት ኩነቶች ላይ ቁጥጥር ባይኖራቸውም በውጤቱ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ይሄውም ሰዎች ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በመተንበይ አሉታዊ ውጤትን በማስወገድ እችል ነበር ብሎ ከማሰብ ሊሆን ይችላል። ይሄ ግን ለውጥ ሳይሆነ ቁጭት ነው።
እራስን ይቅር ማለት ከተፈጠሩት አሉታዊ ክስተቶች ልምድ በመውሰድ ዳግም እንዳይፈጠሩ ትምህርት መውሰድ ነው። ይሄም ትምህርት የተሻለ ማንነትን እንድንጎናጰፍ ያስችለናል።

ይቅር ባይ የመሆን ጥቅሞች

በስነልቦና ውቅር ውስጥ ይቅርታ ሌሎችን እና እራስን ይቅር ማለትን ያካትታል።

ያለፈን የስህተት ህመም መተው እና እራስን ይቅር ማለት ጤናማ የሆነ ስሜትን ከፍ ለማድረግ እና ለራስን ያለን ምልከታ ለማሻሻል ይረዳል። ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ራስን ይቅር ማለትን ሲለማመዱ ዝቅተኛ የመንፈስ ጭንቀት፣ ራስን ለከፍተኛ የስኬት ደረጃዎች ማነቃቃት፣ የተሻለ ውጤታማነት፣ የጠነከረ ትኩረት እና ደስተኛ ህይወትን ይመራሉ። የይቅርታ እንዲሁ በአካላዊ ጤንነት ላይም በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ምርምሮች እንደሚያሳዩት ይቅርታ የኮሌስትሮል መጠንን ሊያሻሽል ይችላል ፤ የሰውነት ህመምን እና የደም ግፊትን መቀነስ እና የልብ ድካም አደጋን ይቀንሳል።

በማጠቃለያ ለራስም ሆነ ለሌሎች ይቅር ማለት። መሸነፍ፣ ደካማ መሆን ወይም ውድቀት አይደለም ነገር ግን የተሻለ ነገን፣ የበለጠ የህይወት ከፍታ ላይ ለመድረስ የትላንትን ስህተት አምኖ እና ተረድቶ እንዲሁም ትምህርት ወስዶ መተው እንጂ። ይሄም ይቅር ባይነት አካላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ጤንነትን ይፈጥራል።

ማሳሰቢያ

ራስን ይቅር ማለቱ ጠቃሚ ልምምድ ቢሆንም ፣ ባልተፈጠረ እና ተጠያቂ ባልሆነቡት ነገር ራሳቸውን አላግባብ ለሚወቅሱ ሰዎች የታሰበ አለመሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

=============================
#ሙዳዬ_ንዋይ_የቢዝነስ_ልህቀት
በትምህርት ያወቅነውን፤ በልምድ ያካበትነውን ፤ አንብበን የተገነዘብነወን የምንጋራበት የማሕበራዊ ገፅ!
ሙዳዬ ንዋይ - የቢዝነስ ልህቀት የዩቲዩብ ቻናል ሰብስክራይብ ማድረግን አይርሱ
   / @sammytekle  

Комментарии

Информация по комментариям в разработке