አንቱ ትልቁ ሰው || በኡስታዝ ሰዒድ አሕመድ || ህዝቡን በእንባ ያራጨ አስገራሚ ግጥም

Описание к видео አንቱ ትልቁ ሰው || በኡስታዝ ሰዒድ አሕመድ || ህዝቡን በእንባ ያራጨ አስገራሚ ግጥም

አንቱ ትልቁ ሰው

የጀማልሁ አሊፍ
ቃላት የሚሟጠው
መቃምሁ ሀው ብቻ
ሁሉን የሚበልጠው
የስምሁ ወገገን
አርሹን ያጊያጊያጠው
ሲዲቅን ጓድ አርጎ ዋሻ ያሰመጠው
ፋሩቅን በዱዐ ከሽርክ ያስመለጠው
ዑስማንን ሰልሎ ኂድማ ያስደፈጠው
ዐሊዩን ተስሩ በኢልሙ ያነጠው
ሐምዛን በዳረንጎ
ኻሊድን ፈልጎ
ቃዕቃዕን ጁንድ አርጎ
ደግሞ አቡ ዱጃናን ጋሻ ጃግሬው አርጎ
አናብስቶች ይዞ ጣጉት ያፈረሰው
ሰው ሆኖ ተወልዶ የተለየ ከሰው
ወሏሂ እኔ እንደ አንቱ
አላውቅም ትልቅ ሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
ዘር ሐረግ ያልሳተው
የእልቅናሁ ስባት
ማዲህ ያዋተተው
የጀማልሁ ግባት
ጥንቱን የፈተተው
የፍልቂትሁ ጥባት
ሽርክ የከተከተው
የኑርሁ ክትባት
ወር መንገድ ሚያባባው
የሃይባሁ ጉልላት
ሊመጠን ሚገደው
የሲሮት ክብባት
ታልቦ አላፈጅም ሲል
አጥቶ ቀረ እልባት
አንቱ ትልቁ ሰው
ተምሞ የጠረቃው
ለዩሱፍ የበቃው
የውበትሁ ጉላት
ዝንቱን የማይደርቀው
እንደ ጣና ሙላት
ማይረግፈው ማይነጥፈው
እንደ አባይ ፍላት

ሲፋ ሆነ ዛትሁ የተሸበረቀው
በመለኮታዊ ክብክብ የጠደቀው
በኑር ተሸብቦ፣ በኑር የታበቀው
ማማር መታመርን
ካንቱ የሸቀቀው
ቁንጅና ቁንጀታን
ካንቱ የተመረቀው
የዝናዎት ብስራት
በኢንጂል በተውራት
ዝንቱን የታወቀው
እንዳንቱ ትልቅ ሰው
የለኝም የማውቀው
አንቱ ትልቁ ሰው
የማንነቶን ሲር
ልሳን የማይጠቅሰው
ፊደል የማይነቅሰው
የግርማዎት ቁንጥር
በነካኩት ቁጥር
በእልህ እየባሰው
መወጠኑም ገዷል
እንኳን ልንጨርሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
የኛ አንጡር ሃብታችን
ዱንያም አኺራችን
ቀን ብራተ ጠሃይ፣ ሌሊት ጨረቃችን
ወረት ርስታችን፣ ጅምርም ማብቂያችን
አንቱ አሉልን ስንል፣ ሌላን መብቃቂያችን
ተግዳር የሌለቦት
አዛዥ አለቃችን
መድህን ሸምጋያችን፣ ዋስም ጠበቃችን
ሰው የመሆን ምስጢር
ከገፍላ መንቂያችን
ወሰንም ኬላችን፣ ባጅ መታወቂያችን
ላጀብ አፍልቆዎት ጌታችን ኸላቁ
ለከውኑ በሙላ አንቱው ኖት ታላቁ

አንቱ ትልቁ ሰው
አፍሁ ማር አዝንቦ
ጥም ሚገረስሰው
የላበቶት ማዛ
ሚስኩን የሚያብሰው
ድምፅሁ በኮለልታው
ሚዝማረ ዳውድን
የሚወሰውሰው
ከዝግ ጆሮ ዘልቆ
አንጀት የሚምሰው
ላይኛውን አለም
በጫማ ያሰሰው
መላኢካ ሊኸድመው
የተርመሰመሰው
ላንቱው ቢሆን እንጂ
አይደል ለሌላው ሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
ዜማየ ቅኝቱ
ሰም ወርቄ ቃላቱ
ቅኔየ አዟሪቱ
ግጥሜ በየ ቤቱ
ቀለሜም ሹለቱ
ክትቤም ወረቀቱ
አንቱው ኖት ሐለቱ
ትልቁ ሰው አንቱ
ሲር ምስጢር አንቱ
የሆንኩትኝ ላንቱ
የሰለምኩት ባንቱ
የተሰተትኩ ካንቱ
የምፅፍ ስላንቱ
የምዞር ወዳንቱ
የማልኖር ያላንቱ
በፍቅር እጅ ያሰጠ
አንድ የለም እንዳንቱ
አንቱ ትልቁ ሰው
የግንባርሁ ጸዳል
ደለማ ሚያብሰው
የጆት ላይ ተአምር
ጨረቃ የገመሰው
ቅርንጫፍ ወደ ሰይፍ
ባንድ የቀለበሰው
ሰራዊት ሊያጠጣ
ጅረት ያፈሰሰው
መዳፎት ላይ ምግቡ
ተስቢህ የወረሰው
የተራቆተን ጋት
ባፍልቅ የዳበሰው
በፍኝ አፈር ንስንስ
ጦሩን ያፈለሰው
ወለፌንድ አንጋዳን
ሜዳ አርጎ የመለሰው
የሂዳያ ከውሰር
ካንቱ የፈሰሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
ዊላዳሁ ሲዘከር
ቦናው የፈረሰው
አብሮት የወጣው ኑር
ሻምን ያዳረሰው
የኪስራን ጉልላት ያንቦለካከሰው
ለሐሊማ ጓዳ ቡራኬን ያዋሰው
ፍቅርሁ ጠቅ አድርጎ
ግዑዝ ሚያንቀሳቅሰው
ግንድ የሚያስለቅሰው
ዛፍ የሚያላውሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
ናፍቆትሁ ቁግ ሆኖ
ጀሰድ የሚጠብሰው
ያለ ገርጋሪ አጋጅ
ለነጠር ሚደርሰው
የመድህዎት ማዱ
አምዛ ሆኖ አጥግቦ
ላንቱ መሆን ጁዱ
እንካ በእንካ አብቦ
ፍቅሮት ኑልኝ ሲል
ማግኔት ሆኖ ስቦ
ናፍቆትዎ ገልጦ
በሰጠር አንብቦ
መጃጅ መጋጀትን
በለህዟ ሚያድሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
ብንከብር ብንከብድም
ብንወጣ ብንወርድም
ብንዘክር ብንኸድም
ብንፆምም ብንሰግድም
ብንበርድም ብንሞቅም
ብንደሳ ብንስቅ፣ ብንበራ ብንደምቅም
ብንጠራ ብንፀድቅም ብንመራ ብንሰብቅም
የዚህ የዚያ ሲሩ
ያንቱ እጅ መሆኑን ፈፅሞ አንደብቅም
ትልቁ ሰው አንቱ
አርሽ ይሁን ጀነቱ
ምድር ሰማያቱ
አእዋፍ አራዊቱ
በጋውም ክረምቱ
መምሸቱም መንጋቱ
ባህሩ ውቂያኖሱ ቲም ብሎ መሙላቱ
ድንጋይ ማመንጨቱ
ክቡር ማዕድናቱ
ሙላው መኽሉቃቱ
ላንቱ አይደል መምጣቱ
አንቱ ትልቁ ሰው
የህላዌ ድምቀት
የኡለሞች እውቀት
የማዲሆች ርቀት
የሙሂቦች ምጥቀት
የጥበባት ጥልቀት
የስብእና እልቀት
ካንቱ ተንቧልቆ
ካላንቱማ ደርቆ
ባንቱው ተፍለቅልቆ
ስላንቱው አፍልቆ
አንቱን ሲል ማቅቆ
ወዳንቱው ሰብቆ
ላንቱ የፈሰሰው
አንቱ ትልቁ ሰው
ፍቅርዎት ሕብራማው
ቀለምን ተቀለም
ተዘር ዘር ማይመርጠው
ተፋሪስ ሰልማንን ያስገዛ ያሸጠው
የሩሙን ሱሃይብን
ና ሲል የገሰጠው
ሎሌውን ቢላልን አሃድ እያስባለ
ወኔውን ያነጠው
አወዳጁ ፍቅርዎት
ጀግናውን ተፈሪ ሴት ተወንድ ሳይነጥል
ሁሉን አርገፍግፎ ሊያነሳ የሚጥል
ቆራርጦ ሚቀጥል
አንድ አርጎ አዋህድ
ሙተየሙን ነቅሶ የሚያቀመጣጥል
የፍቅርዎ ግብር
አጀሙን ተአረብ ፍፁም የማይለየው
ህይወት ያለው በለው ወይ ህይወት የሌለው
በሙላው ተዘርቶ ሙላውን ሚያዋየው

በውድ እጅን ይዞ ቀልብን የሚወርሰው
በከውኑ ላይ አድሮ ፍቅሩ የነገሰው
ወጣቱ አዛውንቱ፣ ወንድ በለው ሴቱ
በክሽን ቃላቱ የሚያቆለባብሰው
ከኔ ነብይ በቀር አላውቅም ተወኝ ሰው
አላውቅም ትልቅ ሰው

አንቱ ትልቁ ሰው
ፍቅርዎት ስር ሰዶ አለም ያዳረሰው
በሙሂቦች ሰርፆ ስንቱን ሆድ ያስባሰው

ናፍቆትሁ አሩሩ መዝምዞ አንገብግቦ
አህመደል ወራቅን ወደ ኸልዋው ስቦ
ቡረዒን ከብክቦ
ሙካሸፋን የሲር ማንገቻ አስነግቦ
የመሃባውን ማድ ዘርግቶ መግቦ
አኒዩን ዳኖችን በኢናያ አጥግቦ
ቡሲሪይ ላይ ዘልቆ
ሐምዚያን ሚሚያን በሌት አስከትቦ
አልከሲዩን መርጦ፣ በካራማ አጅቦ
ሼኽ ዒሳ ቃጥባርን በዙላሉ አርጥቦ
አብደሪዩን የኢልም ዐመል አስረክቦ
ጫሌን በመደድ ድር ላይ ውስጡን ተብትቦ
መድሁን ያስፈሰሰው

አንቱ ትልቁ ሰው

ፍቅርዎት ቅኔ ነው
ገሃድ የተፈታ
ኡመር ሊገድልዎ ሰይፉን የሰለጠው
ፍቅርዎ ውስጥ ውስጡን በስሉ ቢቆርጠው
ያን የጠላት ሰይፉን ጠላት መምተሪያ አርጎ
ባንድ አዳር ለወጠው

ፍቅርዎት ቅኔ ነው
ገሃድ የሰረገ
ሊገድሎት የመጣን ገዳይ ያደረገ

ፍቅርዎ ቅኔ ነው
ሰም ወርቅን ያዘለ
ቢላል ሲያወጣ አዛን ሐምዛ አቤት ስላለ
ጥቁር አስቀድሞ ነጩን ያስከተለ

የፍቅርዎ ቅኔ ገሃድ ወጣ ፈርቁ
ቢላል ሰሙ ሲሆን ሐምዛ ደግሞ ወርቁ

ፍቅርዎ ቅኔ ነው
የሩቅ አንድ አድራጊ
ኑሩን አንፀባርቆ ሙሂብን ፈላጊ
ሰልማንን ከፋሪስ፣
ሱሃይብንም ከሩም
ከከተማ ገጠር ተለክፈው አልቀሩም
ባለ ቅኔው ፍቅሮት ሙሂብን ሲከስብ
በፍቅረ ማግኔቱ ሊያዋህድ የሚስብ

ከሀበሻ አስሃማን በፍቅሩ ሰመመን
ከቻይና ከሂንድም ከግብፅ ከየመን
ማርኳቸው አይደል ወይ
ሊያሳምን ሲነሳ በችኩል ሚታመን

ፍቅርዎ ቅኔ አለው ከኃሊት የማይቀር
በፍቅሩ እያስመሸ በፍቅሩ አስነግቶ
ስብእናን ጥሎ በቅኔው ተዋቀር
ላለማቱ አድሮ ባለም የሚፈቀር

አዎን ያንቱ ብቻ ላይሰክን የጋለው
በዚህ ሲሉት በዚያ መሆን የታደለው
#ALFARUQTUBE

Комментарии

Информация по комментариям в разработке