ማደሪያውን መውደድ መዝሙር 84

Описание к видео ማደሪያውን መውደድ መዝሙር 84

በዘመናችን አይተነው ከማናውቀው ዓለማችንን ከወረረ ብዙዎችን በደዌ ካደቀቀና ሚሊዮኖችን በሞት ከነጠቀ ወረርሽኝ ውስጥ እየወጣን ነው። በዚህ ጊዜ በአካል ተሰብስቦ ማምለክ ስላልተቻለ አቅሙ ያላቸው በቴክኖሎጂ ታግዘው በርቀት ያልቻሉም በቤታቸው ተቀምጠው ከርመዋል። አሁን ግን እንደ ቀድሞው በአካል ተሰባስበን የምናመልክበት በር እየተከፈተ ነው። መሸሸግ ባለብን ጊዜ መሸሸጋችን መልካም ሲሆን በአካል መሰብሰብ ባለብን ጊዜ መሰብሰቡ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በእርግጥ ባደጉት አገራት ለምንኖር በዙም እና በስልክ የምናደርገው ሕብረት ከፍተኛ ምቾት ስላለው ወደ በፊቱ ለመመለስ ጊዜ ሳይወስድብን አይቀርም። ሆኖም የቅዱሳንን በአካል ተገናኝቶ ጸጋ መካፈልን ሊተካ የሚችል ምንም ነገር የለም። ከዚህ በመነሳት ቀደም ሲል በእግዚአብሔር ቃል "ሕዝቤ ሆይ ና! ወደ ቤትህ ግባ! ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ" ሲለን የነበረው ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን አሁን ደግሞ "ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው!" በማለት ወደ አካላዊ ሕብረት እንድንመለስ ይመክረናል። ይህ መዝሙር (መዝ. 84) ከመዝሙሮች ሁሉ እጅጉን የተወደደና በአንድ የእግዚአብሔርን ቤት አደባባዮች በናፈቀ፣ ከቆሬ ልጆች መሐል የሆነ ሌዋዊ በፍቅር፣ በናፍቆት፣ በቅዱስ ቅናት እና በእርካታ የዘመረው ነው። ዛሬ የእግዚአብሔር ማደሪያ በኢየሩሳሌም የሚገኝ መቅደስ ሳይሆን በአቅራቢያችን ያለ የቅዱሳን ሕብረት ነው። ይህም በኢየሩሳሌም ነጭ ድንጋዮች ሳይሆን ከክርስቶስ በተገኘን ሕያዋን ድንጋዬች ተገጣጥሞ የተሠራ ነው። ስለዚህ ብርድ ልብሳችንን ገፈን፣ ከአልጋችን ተስፈንጥረን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ፤ ማደሪያዎቹን (ቅዱሳንን) እንውደድ፣ አብረናቸውም እናምልክ። መልካም የመልዕክት ጊዜ።

Комментарии

Информация по комментариям в разработке